የእብድ ውሻ በሽታ ምልክት መታየቱን ተከትሎ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ክትባት እየሰጠ ነው።
  February 17, 2019    News

የእብድ ውሻ በሽታ ምልክት መታየቱን ተከትሎ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ክትባት እየሰጠ ነው። የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በደሴ ከተማ በደቡብ ወሎና በከሚሴ ብሄረሰብ ዞን ያሉ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ባሏቸው የቤት እንሰሳት ተጠቃሚ እንድሆኑ የተለያዩ ምርምሮችን ከማድረግ ባሻገር የእንሰሳት በሽታ ምልክቶች ሲታዩ የቅድመ መከላከል ክትባቶችን ይሰጣሉ። የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት በደሴና በከምቦልቻ ከተሞች ዙሪያ ተንቀሳቅሶ ባደረገው ቅኝት የዱር ቀበሮዎች በየቦታው እየሞቱ መታየታቸው ከውሻ በሽታ ጋር በቀጥታ የመያያዝ እድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል የት/ቤቱ መምህራኖች ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ከሞቱ ቀበሮዎች በመነሳት ወደ ውሾች በመተላለፍ በቤት እንሰሳትና ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችለውን የውሻ በሽታ ቀድሞ ለመከላከል ት/ቤቱ በማህበረሰብ አገልግሎት ተግባሩ የቅድመ መከላከል ክትባት በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች መስጠት ጀምሯል። የውሻ በሽታን በቅድመ መከላከል ካልሆነ በስተቀር በህክምና ማዳን የማይቻል በመሆኑ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በእንሰሳት ህክምና ት/ቤት የቀረበለትን መረጃ መሰረት በማድረግ ከ220 ሺ ብር በላይ ለመድሀኒት ግዥና ተያያዥ ወጮች በመመደብ ክትባቱ በደሴና በኮምቦልቻ ተሰጥቷል። የውሻ በሽታ በጣም አደገኛ በመሆኑ ቀድመን መከላከል ካልቻልን በእንሰሳትና በሰው ላይም የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ያሉት በዩኒቨርሲቲው የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት ድን ዶ/ር ታረቀኝ ትንታጉ ክትባቱን እየወሰዱ ያሉት ባለቤት ያላቸው የቤት ውሾች ብቻ በመሆናቸው በቀጣይ ባለቤት የሌላቸው የዱር ውሾችን የማስወገድ ስራ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል። አያይዘውም ዶ/ር ታረቀኝ ከውሾች ባለቤት ጋር በመነጋገር የውሾችን የመራባት አቅም ለመቀነስ የወሊድ መከላከያ ክትባት ለመስጠት እንዳቀዱ ተናግረዋል።