በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ።
  February 17, 2019    News

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ። ከህዳር 19/2011 ዓ ም ጀምሮ በፌደራል መንግስት መሪነት በወሎ ዪኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ቀጣይነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ካሉ የተለያዩ አካላቶች ጋር ውይይት ሲካሄድ ቆይቷል። ይህንንም ከሳምንት በላይ ሲካሄድ የነበረ ውይይት ለማሳረግ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላትን በማሳተፍ በዩኒቨርሲቲው ያለውን ሰላም ለማስቀጠል በሚያስችል ሁኔታ የማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሄዷል። ውይይቱን በየደረጃው ሲመሩ የነበሩት የፌደራል መንግስት ተወካይና የግብርና ሚኔስተር ዲኤታ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ከተማሪዎች ከመምህራን ከአስተዳደር ሰራተኞችና ከአካባቢው ማህበረሰብ የተሰጡ አስተያየቶችንና የቀረቡ ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጋር በመወያየት በተቋሙ አቅም የሚፈቱ ተግዳሮቶችን የተቋሙ አመራሮች በችግሮች ክብደት መሰረት በየደረጃው እንድፈቱ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን በመግለጽ ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንድያያቸው የቤት ስራውን መውሰዳቸውን አብራርተዋል። በዚህ የማጠቃለያ ፕሮግራም ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በየደረጃው በተካሄደው ውይይት የተቋማችንን ሰላም ለማስከበር የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ለተቋሙ ሰላም መረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ በተቋሙ የተነሱት አንዳንድ ተግዳሮቶች በእያንዳንዳችን የተቋሙ ማህበረሰብ መፈታት የሚችሉ ሲሆኑ ችግሮቻችንን ወደ ራሳችን በመውሰድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ውጭ በማውጣት የሌሎች አድርጎ የሚታዩበትን አመለካከት በማስወገድ ችግሮቻችንን በሂደት መፍታት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል። መንግስት ከታች ጀምሮ ትውልዱ ግብረ ገብነትን እየተማረ እንድያድግ የትምህርት ስርዓቱን እንዳዲስ ሊፈትሽ ይገባዋል በማለት አስተያየቶችን የሰጡት የሀይማኖት አባቶች የእምነት ተቋማት ሁልጊዜ ሰላምን የሚያስተምሩ ቢሆንም ከ1983 ዓ ም ጀምሮ በመንግስት ሲሰጡ የነበሩ አስተምሮዎች ትውልዱን ከራሱ ጋር ጭምር ያጣሉት በመሆናቸው ሁላችንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሰላምን አስፈላጊነት በማንጸባረቅ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር መታከት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የታዩ የሰላም መናጋቶች በወሎ ያልተከሰተው የወሎ ህዝብ የአስተዳደር በደል ሳይደርስበት ቀርቶ ሳይሆን በወሎ ህዝብ የዘመናት አብሮና ተፈቃቅሮ የመኖር የሰላም እሴት ውጤት ነው ሲሉ ጨምረዋል። በመጨረሻም የሀይማኖት አባቶች የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላም እንድያስቀጥሉ ተሳታፊዎችን እጅ ለእጅ አያይዘው በማስተቃቀፍ ቡራኬ በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።